በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ከሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በመተባበር "ቀጠናዊ ትስስር ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ቃል ዛሬ ጥር 30/2015 ዓ.ም አውደ -ርዕይ አዘጋጅቷል፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራዎቹ ጎን ለጎን መንግስት ትኩረት ለሰጠው ችግር ፈቺ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ትኩረት በመስጠትና የመንግስት የልማት እቅዶችን በጥናት፣ ምርምርና በቴክኖሎጂ ውጤቶች ለመደገፍ እንዲያስችል የተለያዩ የምርምርና የፈጠራ ስራዎች ላይ በማተኮር ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል:: አክለውም የዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር አስፈላጊነቱ እየጨመረ የመጣ ሲሆን ዓላማውም ውስን ሃብትን በጋራ አቀናጅቶ በመጠቀም የጋራ ዓላማን ለማሳካት በመሆኑ የዚህ መሰሉ አውደ -ርዕይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ኢንዱስትሪዎች እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ያላቸውን የተማረ የሰው ኃይል፣ የምርምር ማዕከላትና ቤተ ሙከራዎችን በማቀናጀት የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱ ስራዎችን ከመስራት በዘለለ አላስፈላጊ ድግግሞሽን እና የሃብት ብክነትን ለማስቀረት እንዲሁም ዕውቀትን፣ ልምድን እና የቴክኖሎጂ ፈጠራና ሽግግርን በእጅጉ ያፋጥናል ብለዋል፡፡
የቴክኖሎጂ ሽግግርና የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ባዩ ቡንኩራ በበኩላቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኢንዱስትሪ ትስስር አስፈላጊነትና ስርዓትን በተመለከተ፣ በዩኒቨርሲቲው ሁለት ማዕከላት ማለትም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፓርክ እና የቴክኖሎጂ ቢዝነስ ኢንኩቤሽን ማዕከል መኖሩን፣ እንዲሁም እስከአሁን ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት የተፈጠሩ ትስስሮችን በማስመልከት ሰፋ ያለ ገለፃ አድርገዋል:: የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከኢንዱስትሪ ጋር የሚተሳሰሩበት የማስተማር ማሻሻያ፣ የገንዘብ ድጋፍ፣ መልካም ስም መገንባት እና የኢንዱስትሪ ግንዛቤዎች ማግኘት ላይ መሰራቱን በመግለፅ የዚህ መሰሉ አውደ ርዕይ ደግሞ የእውቀት ሽግግርን ለማድረግ፣ ልምድን ለመለዋወጥና በትብብር ለመስራት ፋይዳው ብዙ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳሉ ሞሲሳ መሰል የፈጠራ ስራዎች አውደ-ርዕዮች የፈጠራ ባህልን ለማሳደግ፣ የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ተሞክሮን ለመለዋወጥ፣ በተመራማሪዎች የሚከወኑ የምርምርና ስርጸት ስራዎችን ለማበራከት፣ አዳዲስ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎችን ለንግድ ስራ ለማስተዋወቅ፣ ከተባባሪና ባለድርሻ ተቋማት ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመፍጠር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ ብለዋል። ም/ዋና ዳይሬክተሩ በሀገራችን የቴክኖሎጂ ሽግግር የተሰማሩት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አዳዲስና የተሻሻሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕውቀቶችን ማመንጨት፣ ጥቅም ላይ ማዋልና የሀገራችንን ህዳሴ ለማረጋገጥ ግንባር ቀደም ተዋንያን ሊሆኑ እደሚገባም አሳስበዋል።
የሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲኑ አቶ መልካሙ ባራሳ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲ፣ቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ኢንዱስትሪዎች መካከል የሚኖረው ግንኙነት እንደ ሀገር ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መሪ ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የሚደረገውን ጉዞ የሚያፋጥን በመሆኑ መሰል ምክክሮች ያስፈልጋሉ ብለዋል። የትምህርትና የምርምር ተቋማት የሚያፈልቋቸውን አዳዲስ የምርምርና የቴክኖሎጂ ስራዎች ተቀብለው ተግባራዊ የሚያደርጉ ኢንዱስትሪዎች ከሌሉ የተሰሩት ስራዎች ትርጉም ስለማይኖራቸው ከኢንዱስትሪዎች ጋር የሚኖር ውጤታማ ግንኙነት የጋራ ስኬትን የሚያመጣ መሆኑንም ገልጸዋል።
በምክክርና አውደ-ርዕዩ በርካታ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለእይታ የቀረቡ ሲሆን፤ የፋሽን ትርኢትና የፓናል ውይይትም ተካሂዷል። በመጨረሻም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲና የሀዋሳ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የጋራ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው መርሃግብሩ ተጠናቋል።